የጽናት ዋጋ ስንት ነው?
በሚካኤል ተሾመ
ጥያቄ ልጠይቅ?! ክርስቲያን ኖት … ካልተሳሳትኩ! ጥያቄዬ ግልጽ የሚሆንሎት ክርስቲያን ከሆኑ ብቻ ነው ብዬ ነወ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወትዎ ዓላማዎ ምንድነው? ካነበቧቸው መጻሕፍት ዓላማ ኖሮት የተሳካለት ሰው ያውቃሉ? አሁን የነገሩኝ ሰው የሕይወት መመሪያዎቹ ምን ምን ናቸው? ዓላማውስ ለመከተል ያደረገው ምንድነው?
ደስታ፤ ሰላም ፤ ሕልም እውን የመሆን፤ የመከራን ክበር፤ ወይስ ምን?.... እስቲ አንዴ በህሊናዎ የርሱን ሕይወት ይቃኙት … ለዚህ ክብር ለመብቃት የተከፈለው መስዋትነት ምን ነበር? እስር ቤት ፤ እንግልት፤ በሰዎች መናቅ፤ ረኃብ… ምን? እነዚህ ሰውን ከዓላማው የሚየስቱ፤ እውነት ብለን ከያዝነው የሚስያክዱ ነገሮች ናቸው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹በፈተና የመጸና የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በíላ ለሚወለዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና›› ይላል፡፡ መከራ ክብር አለው፡፡ ከእያንዳንዱ መከራ ጀርባ ሽልማት አለ፡፡ ችግሩ ግን በእነዚህ መከራዎች መካከል ራስን ደስተኛ ሆኖ ማሰብ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ…›› ሊያሰኝ ይችላል፡፡ ‹‹የማያልፍ የለም …የደስታ ቀን ያልፋል፤ የመከራ ቀንም ያልፋል…›› ብሎ ትዕግስትን ገንዘብ ማድረግ ‹‹ሞኝ በእባብ ሁለቴ ይነደፋል አንዴ ሲያይ›› ሊባል ይችላል፡፡
ዋናው ጥያቄ በመከራ ውስጥ ማን ይጸናል ነው፡፡ ማንስ በፈተና ውስጥ ቀና ብሎ የነገን ሊያይ፤ መልካሙን ሊያስብ፤ ጠላቶቹን ይቅር ሊል ይችላል? መከራ ሲበዛ ይመራል፡፡ በሮች ሁሉ፤ መስኮቶች ሁሉ ዝግ፤ መንገዶች ሁሉ ጠባብ፤ ፍሬዎች ሁሉ መራራ፤ ቀኑ ሁሉ ሌሊት ፤ ምሽቱ ሁሉ የማይነጋ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል፡፡ ይሄን ጊዜ የቅርብ ወዳጃችን እንባችን ይኾናል፡፡
ለዓላማችን ያለን ጽናት በመከራ ይፈተናል፡፡ እምነታችን በሚገጥመን መከራ ይለካል፡፡ ስንዴ ካልሞተች በስብሳ ፍሬ አታፈራም፤ ሰውም በመከራ ካልታሸ ፍሬ አያፈራም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሕይወት ተሞክሯቸው ስለዓላማ ጽናት የሚየሰተመሩንን እናገኛለን ወይም አንብበናል፡፡
ኖኅ አብርሃም፤ ሎጥ ሙሴ፤ ኢያሱ፤ ዳነኤል፤ ኤርሚያስ፤ አሳይያስ፤ ዮሴፍ፤ ቅ/ጳውሎስ… ይቀጥላል፡፡ አንድን ሰው ጽናቱን ለመመዘን፤ ዓላማውን ለማሳት የሚቀርቡት ቅድመ ሁኔታዎች መከራ፤ ጭንቀት፤ ስደት፤ ረኃብ፤ ራቁትነት፤ ፍርሃት ወይም ሰይፍ ሁሉ አላስፈራቸውም፡፡ ያላቸውን ሁሉ ጥለው፤ ትዕግስትን ቤት፤ ተስፋን ግድግዳ፤ እምነትን መሰረት፤ ሰላምን ጣሪያ፤ ፍቅርን ምሰሶ፤ ጽናትና ማገር አድርገው ዓላማቸውን እየተከተሉ ፍኖታቸውን ትተውልን ሄዱ፡፡ ስለዘህም ‹‹ስጋን ከክፉ መሻቱ እና ከምኞቱ ጋራ ሰቀሉ፡፡››
ሙሴ ብድራቱን ትኩር ብሎ ስለተመለከተ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ አለ፤ በዓላማው ጸና፤ አብርሃም የዘመዶቹን ስድብ ሳያስብ እግዚአብሔርን ለመፈለግ የሚሄድበትን ሳያውቅ በእምነት ከቤቱ ወጣ፤ በዓላማው ጸና፡፡
ኖኅ በአሕዛብ መካከል ተቀምጦ ለእግዚኣብሔር ለመገዛት ስለወሰነ የኀጢያተኞችን ስድብ ሳያፍር መርከብን በእምነት አዘጋጀ፤ በኣለማው ጸና፤ ኢያሱ በበረሓው መካካል ‹‹እኔና ቤቴ እግዚኣብሔርን እናመልካለን እናንተ ግን የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ›› አለ ፤ በኣላማው ጸና ፤ ዮሴፍ እግዚኣብሔርን በታማኝነት ማገልገል ከሁሉ የሚሻል መሆኑን ስላወቀ በእስር ቤት ተጥሎ እስከሚረሳ ድረስ አምላኩን አሰበ፤ በዓላማው ጸና፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገጥመን መከራ ሳንደናገጥ ለኣላማችን ተገዥ ብቻ እንድሆን ‹‹ልባችሁ አይታወክ አይፍራም፤ በእኔም እመኑ ፤ በኣባቴም እመኑ›› በማለት መክሮናል፡፡ በዓላማ መጽናት ምንድነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------
ሚካኣል ተሾመ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በህግ ትምህርት የመጀመሪያውን ዲግሪ የያዘ ሲሆን በቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጣና በሌሎችም የህትመት ውጤቶች የተለያዩ ፅሁፎችን በመጻፍ ይታወቃል፡፡
No comments:
Post a Comment