“…. እርሱ እጅግ የሚፈራዊ የራሱን ጥላ ሲያይ ነው….”
በነበረበት ጊዜና ከዚያም በíላ ከተነሱት ነገስታት ሁሉ በጥበቡና በታላቅነቱ ይታወቅ ነበር፤ ታላቁ እስክንድር ገና በሥጋ ዘመኑ አባቱን በመከተል በምክትል ማዕረግ የተወለደበትን ሀገር ይመራ ነበር፡፡ ዕድሜው ወደ አስራስምንት አካባቢ ሲደርስ ታላቅ የጦር መሪ ሊሆን ቻለ፡፡ የመቄዶንያንና ሌሎች ግዛቶችን ደግሞ በ20ኛው ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ በንጉስነት አገለገለ፡፡
እንዲ ሆነ…… አንድ ፊሊኒክስ የተባለ ተሰሎንቄያዊ የነገስታቱን የፈረስ ጋጣ ይጠብቅና ይመራ ዘንድ ኃላፊነት የተሰጠው ሰው ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ ወቅት ወደ ታላቁ እስክንድር አባት ጠጋ ብሎ ከጋጣው ውስጥ ያለ አንድ ፈረስ ለመግራትና ለመጋለብ እምቢ እንዳለ በጣምም ስላስቸገረ ሊሸጥ እንደሚገባ ይመክረው ጀመር፡፡
ይህን መክክር የሰማው ታላቁ እስክንድር በወጣትነት ኃይሉ በመገፋፋት ‹‹ከፊሊኒክስ ጋር ፈረሶቹ ጋጣ ሄጄ ይህንን አውሬ የሆነ ፈረስ ማየት አለብኝ›› ብሎ አባቱን ወተወተ፡፡ አባቱም ስለ ልጁ በመሳሳት እንዳይሄድ ከለከለው፤ ታላቁ እስክንድር ግን ‹‹ አባቴ ሆይ ምንም አልሆንም አትፍራ፤ ይሄ ፈረስ አልገራ ያለበት አንድ ምክንያት ቢኖር ነውና እስቲ እኔ ሄጄ ለመግራት ልሞክረው እባክህን ፍቀድልኝ?›› ብሎ በድጋሚ አባቱን ለመነ ንጉሱም ‹‹ከፊሊኒክስ የበለጠ የመግራት ልምድ ያለህ አይመስለኝም ፊሊኒክስ እድሜውን በሙሉ እንስሳትን በመግራትና በማለማመድ እንደቆየ ልብ በል›› አለው፤ እስክንድርም መልሶ ‹‹ አባቴ ሆይ ልክ ብለሃል ፈረሶቹን የመግራት ልምድ የለኝም ፡ ግን የዚህን አውሬ የሆነ ፈረስ ፀባይ እና እምቢ ባይነቱን ማወቅ አለብኝ፡፡›› ብሎ መለሰለት፡፡
ወጣቱ እስክንድርም ወደ ታላቁ ቤተመንግስት ፈረስ ጋጣ ከፊሊኒክስ ጋር አመራ ፊሊኒክስም ወደ አስቸጋሪው ፈረስ ጠጋ ብሎ ለመያዝና ለመግራት ሲሞክር በጋጣው ውስጥ የነበረ ግርግርና የፈረሱ ማስቸገር እጅግ በዛ፡፡ በዚህ ጊዜ ወጣቱ እስክንድር በፍጥነት የፈረሱን ልጓም በመያዝ ከነበረበት አቅጣጫ አዞረው፤ ወዲያውኑ አስቸጋሪው ፈረስም ተረጋጋ ለዘብም አለ፡፡ እስክንድርም በተረጋጋ መንፈስ ፈረሱን አሰለጠነው፤ ጋለበውም ፈረሱንም እየጋለበ ወደ አባቱ ዘንድ ወሰደው፡ አባቱም በልጁ ጥበብ በመደነቅ በዚች ትንሽ ጊዜ ውስጥ አስቸጋሪውን ፈረስ በመግራቱ በመገረም ‹‹ልጄ እስክንድር ሆይ ምን ጥበብ ብትጠቀም ነው እንዲ የተገራልህ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ እስክንድርም ‹‹አባቴ ሆይ ነገሩ ቀላል ነው፡ ፈረሱ ሁልጊዜ ከፊት ለፊት የራሱን ጥላ ሲያይ እጅግ ይፈራል፤ በዚህ ጊዜም ያስቸግራል፤ ስለዚህ የፈረሱን ልጓም ይዤ ፊቱን ወደ ፀሀይ አቅጣጫ አዞርኩት፤ ይሄኔም የራሱ ጥላ በእግሮቹ ኮቴ ስር ሲሆን መፍራቱንም ማስቸገሩንም ተወ ተረጋጋ›› ብሎ መለሰለት፡፡
እውነት ነው…….በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህዝቦች የራሳቸውን ጥላ ሲያዩ ይፈራሉ፡፡ ነገር ግን አይናቸውን ወደ ፀሀይ ፅድቅ ቢያዞሩ ጥላ የሚባለውን ፍራቻ ከቶ አያዩም፤ጥላቸውም በእግራቸው ኮቴ ስር ይወድቃል፤ ፍርሀቱም በእምነትና በእግዚአብሔር ጥባቆት ይተካል፡፡
ወደ ክርስቶስ እንቅረብ … እርሱ ፀሀየ ፅድቅ ነውና ጥላችንን በእግራችን ስር ይጥለዋል፡፡ የጌታን ድምጽ በተለይም ‹‹ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው….. ብርሃን ሰላላችሁ ተመላለሱ …..የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ስላላችሁ በብርሃን እመኑ›› ዮሐ 12፡35-36 /የሚለውን ትሰማላችሁ፡፡
የፅድቅ ፀሐይ ሆይ ለነፍሴ ብርሀንን ስጣት፤ ብርሃንህንም ባየች ጊዜ ጥላዋ በእግሮችዋ ኮቴ ስር ይወድቃሉ ያን ጊዜም ….የራሴን ጥላ መፍራት አልጀምርም፡፡
ምንጭ ፡ spring of love
ከብሥራት መጽሔት ቁጥር 23 አራተኛ አመት 2001 ዓ.ም የተወሰደ ዮሴፍ አረጋ
No comments:
Post a Comment